18 አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስ ጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር።
19 እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዶአል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው።
20 ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤
21 አሁን ግን እንዴት ማየት እንደቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።”
22 ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኲራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው።
23 ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ።
24 ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት።