20 ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቶአል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቶአል፤
21 አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።”
22 ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ቆመ ነበር።
23 አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህን?
24 አምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ አምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን አትምርምን?
25 እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?”
26 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “በሰዶም ከተማ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ።