ዘፍጥረት 24 NASV

የይስሐቅና የርብቃ ጋብቻ

1 በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው።

2 አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤

3 ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ማልልኝ።

4 ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።”

5 አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው።

6 አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤

7 ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ።

8 ሴቲቱ አብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው።

9 ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጐ ስለዚህ ጒዳይ ማለለት።

10 አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዙ።

11 እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ጥላ የበረደበት፣ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነበር።

12 ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጒዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው፤

13 እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ።

14 እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”

15 እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች።

16 ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች።

17 አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።

18 እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው።

19 እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች።

20 ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጒድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው።

21 አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዱን አሳክቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጂቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር።

22 ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣

23 “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት።

24 እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤

25 ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው።

26 ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ፤

27 እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተመሰገነ ይሁን።”

28 ልጂቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች።

29 ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጒድጓድ ፈጥኖ ሄደ።

30 እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤

31 እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው።

32 ሰውየው ከላባ ጋር ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለእርሱና አብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው።

33 ለሰውየውም ማዕድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጒዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ።ላባም፣ “እሺ፤ ተናገር” አለው።

34 እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤

35 እግዚአብሔር (ያህዌ) ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል።

36 የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል።

37 ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፤ ‘ከዚህ ከምኖርበት አገር፣ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር ልጄን አታጋባው፤

38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት’።

39 “እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት።

40 “እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል።

41 ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጂቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ።

42 “እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጒድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጒዳይ አቃናልኝ፤

43 እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣

44 እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’

45 “በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት።

46 “እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሸዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች።

47 “ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ” ብዬ ጠየቅኋት።“እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ።“ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት።

48 ተደፍቼም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝ የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አመሰገንሁ።

49 እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።”

50 ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም።

51 ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።”

52 የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ።

53 ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው።

54 እርሱና አብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤በማግስቱ ጠዋት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ።

55 ወንድሟና እናቷም፣ “ልጂቷ ከእኛ ጋር ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ።

56 እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው።

57 እነርሱም፣ “ለማናቸውም ልጂቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ።

58 ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት።እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች።

59 ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋር፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው።

60 ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤“እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”።

61 ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ።

62 በዚህን ጊዜ፣ ይስሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር።

63 እርሱም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ።

64 ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይስሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤

65 አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው።አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች።

66 አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው።

67 ይስሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባትም፤ ሚስት ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50