ዘፍጥረት 25 NASV

የአብርሃም መሞት

1 አብርሃም ኬጡራ የተባለች ሌላ ሚስት አገባ።

2 እርሷም፦ ዘምራንን፣ ዮቅሳንን፣ ሜዳንን፣ ምድያምን፣ የስቦቅንና ስዌሕን ወለደችለት።

3 ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ፤ የድዳንም ልጆች፦ አሦራውያን፣ ለጡሳውያንና ለኡማውያን ናቸው።

4 የምድያም ልጆች፦ ጌፌር፣ ዔፌር፣ ሄኖኅ፣ አቢዳዕና ኤልዳድ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።

5 አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤

6 ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው፤ ከልጁ ከይስሐቅም ርቀው እንዲኖሩ ወደ ምሥራቅ ምድር ሰደዳቸው።

7 አብርሃም በጠቅላላው መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ።

8 ከዚያም ዐረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

9 ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል በመምሬ አጠገብ በምትገኝ በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን ዕርሻ በመክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤

10 ይህም የዕርሻ ቦታ አብርሃም ከኬጢያውያን የገዛው ነበር፤ ከሚስቱ ከሣራ አጠገብ በዚያ ተቀበረ።

11 አብርሃም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይስሐቅን ባረከው፤ በዚህ ጊዜ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮኢ አቅራቢያ ይኖር ነበር።

የእስማኤል ልጆች

12 ግብፃዊቷ የሣራ አገልጋይ አጋር፣ ለአብርሃም የወለደችለት የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው።

13 የእስማኤል ልጆች ስም እንደ ዕድሜያቸው ቅደም ተከተል እንዲህ ነው፦ የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፣ ቄዳር፣ ነብዳኤል፣ መብሳም፣

14 ማስማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣

15 ኩዳን፣ ቴማን፣ ኢጡር፣ ናፌስና ቄድማ።

16 እነዚህ የእስማኤል ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም በኖሩባቸውና በሰፈ ሩባቸው ቦታዎች የዐሥራ ሁለት ነገድ አለቆች ስሞች ናቸው።

17 እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

18 ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።

ያዕቆብና ዔሳው

19 የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤

20 ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።

21 ይስሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች።

22 ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለመጠየቅ ሄደች።

23 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤“ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት።

24 የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀንዋ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ።

25 በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጒር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ።

26 ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይስሐቅ የሥልሳ ዓመት ሰው ነበር።

27 ልጆቹም አደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር።

28 ይስሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።

29 አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ።

30 ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ።

31 ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው።

32 ዔሳውም፣ “እነሆ፣ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ።

33 ያዕቆብም ዔሳውን፣ “እንግዲያማ፣ አስቀድመህ ማልልኝ” አለው፤ ስለዚህም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠለት።

34 ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ እርሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ።ዔሳው ብኵርናውን እንዲህ አድርጎ አቃለላት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50