ዘፍጥረት 27 NASV

ይስሐቅ ያዕቆብን ባረከው

1 ይስሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው።እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።

2 ይስሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን ዐላውቅም

3 ስለዚህ የአደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰሮጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ።

4 ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።”

5 ይስሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣

6 ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣

7 ‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤

8 ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ።

9 ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ፣ የሚወደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤

10 እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ፣ ይዘህለት ግባና ይብላ።”

11 ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጒራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው።

12 ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።”

13 እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።

14 እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት።

15 ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው።

16 እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው።

17 ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው።

18 ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ፤ አለ፤ ይስሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው።

19 ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስቲ ቀና በልና እንድትመርቀኝ አድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ።

20 ይስሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀናህና መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት።

21 ይስሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በእርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስቲ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው።

22 ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ።

23 እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጒራም ስለሆኑ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው።

24 ይስሐቅም፣ “በእርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ።

25 ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ አድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም።

26 ከዚያም አባቱ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው።

27 ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ባረከው፣እንደ መስክ መዐዛ ነው።

28 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰማይን ጠል፣የምድርንም በረከት፣የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ።

29 መንግሥታት ይገዙልህ፤ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።”

30 ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ።

31 እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው።

32 አባቱ ይስሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው።

33 በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በእርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው።

34 ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው።

35 ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።

36 ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።

37 ይስሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት።

38 ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

39 አባቱ ይስሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤“መኖሪያህከምድር በረከት፣ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤

40 በሰይፍ ትኖራለህ፤የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ።አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣ወዲያ ትጥላለህ።”

ያዕቆብ ወደ ላባ ሸሸ

41 አባቱ ያቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቦአል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ አሰበ።

42 ርብቃ፣ ታላቁ ልጇ ዔሳው ያሰበው በተነገራት ጊዜ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ጊዜ እየጠበቀ ነው፤

43 አሁንም፣ ልጄ ሆይ፤ እኔ የምልህን አድርግ፤ በካራን ምድር ወደሚኖረው ወደ ላባ ቶሎ ሽሽ።

44 የወንድምህ ቍጣ እስከሚበርድ እዚያው ቈይ፤

45 ነገር ግን ቍጣው በርዶለት ያደረግህበትን ከረሳ በኋላ፣ እንድትመለስ እልክብህና ትመጣለህ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?”

46 ከዚያም ርብቃ ይስሐቅን፣ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50