1 ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ስለዚህ ያዕቆብን፣ “ልጅ ስጠኝ፤ አለበለዚያ እሞታለሁ” አለችው።
2 ያዕቆብም ራሔልን ተቈጥቶ “እኔ እንዳትወልጂ ያደረገሽን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መሰልኹሽን?” አላት።
3 እርሷም፣ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው።
4 ስለዚህም አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ፤
5 እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።
6 ራሔልም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ አወጣችለት።