ዘፍጥረት 48:16-22 NASV

16 ከጒዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤እነርሱም በስሜ፣በአባቶቼ በአብርሃምናበይስሐቅ ስም ይጠሩ፤በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።

17 ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤

18 ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም በኵሩ ይህኛው ስለ ሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው።

19 አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እምቢ አለው።

20 በዚያን ዕለት ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤“በአንተ ስም እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመርቃል፤“እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ።”በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።

21 ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል።

22 እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኳትን ዐምባ ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”