13 አስከሬኑን ወደ ከነዓን ምድር ወስደው አብርሃም ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ላይ ከነዕርሻው በገዛው፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት።
14 ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ፣ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር አብረውት ሄደው ከነበሩት ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ተመለሰ።
15 የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ።
16 ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤
17 ‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም፣ የእኛን የአባትህን አምላክ (ኤሎሂም) አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ።
18 ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት።
19 ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ቦታ ማን አስቀመጠኝ?