1 ንጉሥ ቤልሻዛር ለሺህ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር።
2 ቤልሻዛር የወይን ጠጁን እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ።
3 ከዚያም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ መጠጫዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹም ጠጡባቸው።
4 የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገኑ።
5 በድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤
6 በዚያን ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጒልበቶቹም ተብረከረኩ።
7 ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቈጣሪዎችንና መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጒሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ ላይ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።”
8 ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብም ሆነ ትርጒሙ ምን እንደሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም።
9 ንጉሥ ቤልሻዛር ከፊት ይልቅ ፈራ፤ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቶአቸው ተደናገጡ።
10 ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ አትደንግጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ!
11 በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል፣ ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቶአል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቈጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው።
12 ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ እንቆቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጒም ይነግርሃል።”
13 ዳንኤልንም ወደ ንጉሡ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን?
14 የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤
15 ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጒሙ ምን እንደሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፤ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም።
16 አንተ ግን መተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጒሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ያለብሱሃል፤ የወርቅ ሐብል በዐንገትህ ያጠልቁልሃል፤ የመንግሥት ሦስተኛ ገዥም ትደረጋለህ።”
17 ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጒሙ ምን እንደሆነም እነግረዋለሁ።
18 “ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው።
19 ከሰጠው ታላቅ ሥልጣን የተነሣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም ሁሉ ተንቀጠቀጡለት፤ ፈሩትም። ንጉሡም ሊገድል የፈለገውን ይገድል፣ ሊያድን የፈለገውን ያድን፣ ሊሾም የፈለገውን ይሾም፣ ሊያዋርድ የፈለገውንም ያዋርድ ነበር።
20 ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ።
21 ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋር ኖረ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነርሱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
22 “ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤
23 ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም።
24 ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን የጻፈውን እጅ ላከ።
25 “የተጻፈውም ጽሕፈት፣‘ማኔ፣ ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” ይላል።
26 “የቃሉም ትርጒም ይህ ነው፤‘ማኔ’ ማለት እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቈጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አደረሰው ማለት ነው።
27 ‘ቴቄል’ ማለት በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም ተገኘህ፣ ማለት ነው።
28 ‘ፋሬስ’ ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።
29 ከዚህ በኋላ በቤልሻዛር ትእዛዝ ዳንኤልን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለበሱት፣ የወርቅ ሐብል በዐንገቱ ላይ አጠለቁለት፤ የመንግሥቱም ሦስተኛ ገዥ ሆኖ ተሾመ።
30 በዚያኑ ሌሊት የባቢሎናውያን ንጉሥ ቤልሻዛር ተገደለ፤
31 የሥልሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስም መንግሥቱን ወሰደ።