2 ዳዊትም፣ “አባቱ ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረገልኝ እስቲ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን በጎ ነገር ላድርግለት” ብሎ አሰበ። ስለዚህ ዳዊት ስለ አባቱ ሞት ሐዘኑን ለመግለጽ ወደ ሐኖን መልክተኞችን ላከ። የዳዊት ሰዎች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ሐኖን ወደሚኖርበት ወደ አሞናውያን ምድር በመጡ ጊዜ፣
3 የአሞናውያን መኳንንት ለሐኖን “ዳዊት ሐዘኑን ለመግለጽ ሰዎችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃልን? ሰዎቹ ወደ አንተ የመጡት አገሪቱን ለመመርመር፣ ለመሰለልና ለመያዝ አይደለምን?” አሉት።
4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ መኻል ለመኻል ቀዶ ሰደዳቸው።
5 በሰዎቹ ላይ የደረሰባቸውን ዳዊት በሰማ ጊዜ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር፣ ወደ እነርሱ መልክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ትመጣለችሁ” አለ።
6 አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባወቁ ጊዜ፣ ሐኖንና አሞናውያን ከመስጴጦምያ፣ ከአራም መዓካና ከሱባ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመከራየት አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ፤
7 ከዚያም ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን እንዲሁም የመዓካን ንጉሥና ወታደሮች በገንዘብ ቀጠሩ፤ እነርሱም መጥተው በሜድባ አጠገብ ሲሰፍሩ፣ አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት ወጡ።
8 ዳዊት ይህን ሲሰማ ኢዮአብንና መላውን ተዋጊ ሰራዊት ላከ።