1 ዜና መዋዕል 19:3-9 NASV

3 የአሞናውያን መኳንንት ለሐኖን “ዳዊት ሐዘኑን ለመግለጽ ሰዎችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃልን? ሰዎቹ ወደ አንተ የመጡት አገሪቱን ለመመርመር፣ ለመሰለልና ለመያዝ አይደለምን?” አሉት።

4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ መኻል ለመኻል ቀዶ ሰደዳቸው።

5 በሰዎቹ ላይ የደረሰባቸውን ዳዊት በሰማ ጊዜ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር፣ ወደ እነርሱ መልክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ትመጣለችሁ” አለ።

6 አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባወቁ ጊዜ፣ ሐኖንና አሞናውያን ከመስጴጦምያ፣ ከአራም መዓካና ከሱባ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመከራየት አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ፤

7 ከዚያም ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን እንዲሁም የመዓካን ንጉሥና ወታደሮች በገንዘብ ቀጠሩ፤ እነርሱም መጥተው በሜድባ አጠገብ ሲሰፍሩ፣ አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት ወጡ።

8 ዳዊት ይህን ሲሰማ ኢዮአብንና መላውን ተዋጊ ሰራዊት ላከ።

9 አሞናውያንም መጥተው ወደ ከተማቸው በሚያስገባው በር ላይ ለጦርነት ተሰለፉ፤ የመጡት ነገሥታት ደግሞ ብቻቸውን በሜዳው ላይ ነበሩ።