15 እንግዶች አማልክትንና ጣዖታቱን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ኰረብታና በኢየሩሳሌም የሠራቸውንም መሠዊያዎች ሁሉ አራቀ፤ ከከተማዪቱም ውጭ ጣላቸው።
16 ከዚያም የእግዚአብሔርን መሠዊያ ዐደሰ፤ በላዩም የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አዘዘ።
17 ሕዝቡ ግን በኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መሠዋቱን ቢቀጥልም፣ የሚሠዋው ግን ለአንዱ አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።
18 በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ወደ አምላኩ ያቀረበው ጸሎቱና ባለ ራእዮች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት ቃል በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።
19 ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጒደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለ ራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል።
20 ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
21 አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሁለት ዓመት ገዛ።