ሐዋርያት ሥራ 15:3-9 NASV

3 ቤተ ክርስቲያኒቱም እግረ መንገዳቸውን በፊንቄና በሰማርያ በኩል እንዲያልፉ ላከቻቸው፤ እነርሱም በእነዚህ ቦታዎች ለነበሩት የአሕዛብን መመለስና ማመን ነገሯቸው፤ ወንድሞችም ሁሉ በዚህ እጅግ ደስ አላቸው።

4 ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት እንዲሁም ሽማግሌዎች ተቀበሏቸው፤ የተላኩትም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሠራውን ሁሉ ነገሯቸው።

5 ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው በመቆም፣ “አሕዛብ እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው” አሉ።

6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጒዳይ ለማጤን ተሰበሰቡ።

7 ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ።

8 ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤

9 ልባቸውንም በእምነት በማንጻት በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም።