39 በነጋም ጊዜ፣ ወደ የብስ መቅረባቸውን አላወቁም ነበር፤ ነገር ግን ዳር ዳሩ አሸዋማ የሆነ የባሕር ሰርጥ አይተው፣ ቢቻላቸው መርከቡን ገፍተው ወደዚያ ለማድረስ ወሰኑ።
40 ከዚያም መልሕቆቹን ቈርጠው ባሕር ውስጥ ጥለው ሄዱ፤ የመቅዘፊያውንም ገመድ በዚያው ጊዜ ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ባሕሩ ዳርቻ አቀኑ።
41 ነገር ግን መርከቡ ከአሸዋ ቍልል ጋር ተላትሞ፤ መሬት ነካ፤ የፊተኛው ክፍሉም አሸዋው ውስጥ ተቀርቅሮ አልነቃነቅ አለ፤ የኋለኛው ክፍሉም በማዕበሉ ክፉኛ ስለ ተመታ ይሰባበር ጀመር።
42 ወታደሮቹም ከእስረኞች ማንም ዋኝቶ ለማምለጥ ቢሞክር ለመግደል ተስማሙ።
43 የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ እንዲተርፍ ስለ ፈለገ፣ ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው፤ መዋኘት የሚችሉ ከመርከብ እየዘለሉ አስቀድመው ከባሕሩ ወደ ምድር እንዲወጡ፣
44 የተቀሩት ደግሞ በሳንቃዎች ወይም በመርከቡ ስብርባሪ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።