33 እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”
34 ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
35 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ?
36 ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ጌታ ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው።” ይላል፤
37 ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።
38 በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤
39 በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፣ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤