9 ‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት ራሳችሁን አታታሉ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣ ይችላል እላችኋለሁና።
10 እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቶአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።
11 “እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም የማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ኀያል ከእኔ በኋላ ይመጣል። እርሱም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።
12 መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውን ያጠራል፤ ስንዴውን በጐተራ ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”
13 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
14 ዮሐንስ ግን፣ “ይህማ አይሆንም፤ እኔ ባንተ መጠመቅ ሲያስፈልገኝ እንዴት አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ተከላከለ።
15 ኢየሱስም፣ “ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው፤ ዮሐንስም በነገሩ ተስማማ።