ራእይ 18:10-16 NASV

10 ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤“አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ!”አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቶአል።”

11 “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤

12 ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣

13 ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው።

14 እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቆአል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቶአል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም” ይላሉ።

15 እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤

16 ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤“ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!