1 ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፣ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን አብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው።
2 ዳዊት፣ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፣ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ።
3 ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።”
4 ካህኑም፣ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፣ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው።
5 ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ ባል ተቀደሰ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ታዲያ ዛሬማ እንዴት!” ሲል መለሰ።
6 ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከእግዚአብሔር ፊት ተነሥቶ በትኩስ እንጀራ ከተተካው ከኅብስተ ገጹ በስተቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና።
7 በዚያችም ዕለት ከሳኦል አገልጋዮች አንዱና የእረኞቹ አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያው በእግዚአብሔር ፊት እንዲቈይ ተገዶ ነበር።