1 ዜና መዋዕል 11:16-22 NASV

16 በዚያን ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ደግሞ በቤተልሔም ነበረ።

17 ዳዊትም ውሃ ፈልጎ ነበርና፣ “ከቤተ ልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ።

18 በዚህ ጊዜ ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ጥሰው በማለፍ በቤተልሔም በር አጠገብ ከሚገኘው ጒድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው፤

19 ከዚያም “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?” አለ። ይህን ለማምጣት በሕይወታቸው ቈርጠው ስለ ነበር፣ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም።ሦስቱ ኀያላን ሰዎች የሠሩት ይህንን ነበር።

20 የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎች ገደለ፤ ከዚህም የተነሣ እንደ ሦስቱ ሁሉ ዝነኛ ሆነ።

21 ከሦስቱ አንዱ ሆኖ ባይቈጠርም እንኳ፣ እጥፍ ክብር አገኘ፤ አዛዣቸውም ሆነ።

22 ከቀብስኤል የመጣውና ታላቅ ጀብዱ የሠራው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ብርቱ ተዋጊ ነበረ። እርሱም እጅግ የታወቁ ሁለት የሞአብ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም አንድ ጊዜ በረዶ ምድርን በሸፈነበት ቀን ወደ አንድ ጒድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ።