1 ነገሥታት ለጦርነት በሚሄዱበት በጸደይ ወራት፣ ኢዮአብ የጦር ሰራዊቱን እየመራ ሄዶ የአሞናውያንን አገር አጠፋ፤ ወደ ራባትም ሄዶ ከበባት፤ ዳዊት ግን ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። ኢዮአብም ራባትን ወግቶ አፈራረሳት፤
2 ዳዊት የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ነበረ፤ ይህንንም በዳዊት ራስ ላይ ጫኑለት፤ እንዲሁም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ።
3 በዚያ የነበረውንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ ዶማና መጥረቢያ ይዘው እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊት በሌሎቹም የአሞን ከተሞች ሁሉ ይህንኑ አደረጉ። ከዚያም ዳዊትና መላው ሰራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
4 ከዚያም በኋላ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በጌዝር ጦርነት ተደረገ፤ በዚያ ጊዜ ኩሳታዊው ሴቦካይ የራፋይም ዘር የሆነውን ሲፋይን ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ድል ተመቱ።