1 ዜና መዋዕል 21:16-22 NASV

16 ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ።

17 ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የበደልሁት እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።

18 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።

19 ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል መሠረት ለመፈጸም ወጣ።

20 ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ አብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ።

21 ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርና ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ።

22 ዳዊትም፣ “በሕዝቡ ላይ የወረደው መቅሠፍት እንዲወገድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ዐውድማህን ልውሰደው፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።