1 ዜና መዋዕል 22:14-19 NASV

14 “ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሆንም አንድ ሺህ መክሊት ወርቅ፣ አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፣ ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ለማዘጋጀት በተቻለኝ ሁሉ ጥሬአለሁ። በተረፈ አንተ ጨምርበት።

15 ድንጋይ ጠራቢዎች፣ ግንበኞች፣ አናጢዎች የሆኑ ብዙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ የተጠበቡ ሰዎች አሉህ፤

16 እነዚህም ቊጥራቸው እጅግ የበዛ የወርቅ፣ የብር፣ የናስና የብረት ሠራተኞች ናቸው። በል ሥራህን ጀምር፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።”

17 ከዚያም ዳዊት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ልጁን ሰሎሞንን እንዲረዱት አዘዘ፤

18 እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር አምላካችሁ እስካሁን ከእናንተ ጋር አይደለምን? በየአቅጣጫውስ ዕረፍትን ሰጥቷችሁ የለምን? የምድሪቱን ነዋሪዎች በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኛል፤ ምድሪቱም ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ተገዝታለች።

19 አሁንም እግዚአብሔር አምላካችሁን ለመፈለግ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ሰብስቡ። የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦትና ንዋያተ ቅድሳቱን ለእግዚአብሔር ስም ወደሚሠራው ቤተ መቅደስ አምጥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”