1 ዜና መዋዕል 26:28-32 NASV

28 ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉና እንዲሁም ሌሎቹን ንዋያተ ቅድሳት ሰሎሚናትና ቤተ ዘመዶቹ ይጠብቁ ነበር።

29 ከይስዓራውያን፤ ከናንያና ወንዶች ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ባለው ሥራ በእስራኤል ላይ ሹማምትና ዳኞች ሆነው ተመደቡ።

30 ከኬብሮናውያን፤ ሐሽብያ፣ ጠንካራና ጐበዝ የሆኑ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው የእስራኤል ምድር ላለው የእግዚአብሔር ሥራና ለንጉሡም አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ።

31 በኬብሮናውያን በኩል በቤተ ሰቦቻቸው የትውልድ መዝገብ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበረ። በዳዊት ዘመነ መንግሥት በአርባኛው ዓመት መዛግብቱ ተመርምረው ስለ ነበር፣ በገለዓድ ውስጥ ኢያዜር በተባለ ቦታ ከኬብሮናውያን መካከል ጠንካራ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል።

32 ይሪያም ጠንካሮችና የቤተ ሰባቸው አለቆች የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሥጋ ዘመዶች ነበሩት። ንጉሥ ዳዊትም እነዚህን የእግዚአብሔር ለሆነውና የንጉሡም በሆነው ጒዳይ ላይ ሮቤልን፣ ጋድንና የምናሴን ነገድ እኵሌታ ኀላፊ አድርጎ ሾማቸው።