1 ዜና መዋዕል 29:1-5 NASV

1 ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ለመላው ጉባኤ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ወጣትና ልምድም የሌለው ነው። ይህ ታላቅ ሕንጻ የሚሠራው ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር አምላክ በመሆኑ፣ ሥራው ከባድ ነው።

2 እኔም ያለኝን ሀብት ለአምላኬ ቤተ መቅደስ ለወርቁ ሥራ ወርቁን፣ ለብሩ ሥራ ብሩን፣ ለናሱ ሥራ ናሱን፣ ለብረቱ ሥራ ብረቱን፣ ለዕንጨቱ ሥራ ዕንጨቱን እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን መረግድ፣ ኬልቄዶን፣ ልዩ ልዩ ኅብር ያላቸውን የከበሩ ድንጋዮች፣ ማናቸውንም ዐይነት የሚያምር ድንጋይና ዕብነበረድ፣ ይህን ሁሉ በብዛት አዘጋጅቻለሁ።

3 ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤

4 ይህም ሦስት ሺህ መክሊት የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺህ መክሊት ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ

5 እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በባለ ሙያዎች ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?”