1 ዜና መዋዕል 5:17-23 NASV

17 እነዚህ ሁሉ በትውልድ መዝገብ የሰፈሩት በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታምና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነው።

18 የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ብቁ የጦር ሰዎች ነበሩአቸው። እነርሱም ጋሻ መያዝ፣ ሰይፍ መምዘዝና ቀስት መሳብ የሚችሉ ጠንካራና በውጊያ የሠለጠኑ ናቸው።

19 እነዚህም በአጋራውያን፣ በኢጡር፣ በናፌስ፣ በናዳብ ላይ ዘመቱ።

20 በጦርነቱም ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው ስለ ነበር፣ በውጊያው ረዳቸው፤ አጋራውያንንና የጦር አጋሮቻቸውን ሁሉ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ስለ ታመኑበትም ጸሎታቸውን ሰማ።

21 የአጋራውያንንም እንስሶች ማረኩ፤ እነዚህም አምሳ ሺህ ግመሎች፣ ሁለት መቶ አምሳ ሺህ በጎችና ሁለት ሺህ አህዮች ነበሩ። እንዲሁም አንድ መቶ ሺህ ሰው ማረኩ።

22 ውጊያው የእግዚአብሔር ስለ ነበር ሌሎችም ብዙ ሰዎች ተገደሉ። እስከ ምርኮ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ በእጃቸው ነበረች።

23 የምናሴ ነገድ እኩሌታ ሕዝብ ቍጥር ብዙ ነበረ፤ እነርሱም ከባሳን ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔም ድረስ ባለው ምድር ሰፈሩ፤ ይህም እስከ ሳኔር አርሞንዔም ተራራ ድረስ ማለት ነው።