2 ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብፅ ተመልሶ መጣ።
3 እርሱንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም ሄደው እንዲህ አሉት፤
4 “አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን።”
5 ሮብዓምም፣ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ።
6 ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም፣ “ለዚህ ሕዝብ ምን እንድመልስለት ትመክሩኛላችሁ?” በማለት አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ ያገለገሉትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠየቃቸው።
7 እነርሱም፣ “ለእዚህ ሕዝብ ደግ ከሆንህለት፣ ደስ ካሰኘኸውና የሚስማማው መልስ ከሰጠኸው ምንጊዜም ይገዛልሃል” አሉት።
8 ሮብዓም ግን ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ትቶ፣ አብሮ አደጎቹና አገልጋዮቹ ከሆኑት ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤