14 ኢዮርብዓምና ልጆቹ ሌዋውያኑን ከእግዚአብሔር የክህነት አገልግሎት ስላባረሯቸው ሌዋውያኑ ማሰማሪያ ቦታቸውንና ንብረታቸውን ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤
15 እርሱም ለየኰረብታው መስገጃ እንዲሁም ለሠራቸው የፍየልና የጥጃ ምስሎች የራሱን ካህናት ሾመ።
16 ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ ከልባቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ።
17 በዚሁ ሁኔታ የዳዊትንና የሰሎሞንን መንገድ በመከተል፣ ለሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምንም ረዱ።
18 ሮብዓም መሐላትን አገባ፤ አባቷ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ሲሆን፣ እናቷም አቢካኢል የተባለች፣ የእሴይ የልጅ ልጅ የኤልያብ ልጅ ነበረች።
19 እርስዋም የዑስ፣ ሰማርያና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።
20 ከዚያም የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያ፣ ዓታይ፣ ዚዛ፣ ሰሎሚት የተባሉትን ወለደችለት።