2 ዜና መዋዕል 13:11-17 NASV

11 እነርሱም በየጧቱና በየማታው የሚቃጠል መሥዋዕትና ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የገጹን ኅብስት በሥርዐቱ መሠረት በነጻው ጠረጴዛ ላይ ያኖራሉ፤ በየማታውም በወርቁ መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል።

12 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ መሪአችንም እርሱ ነው። መለከት የያዙ ካህናቱም የጦርነቱን ድምፅ በእናንተ ላይ ያሰማሉ። እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ አይቀናችሁምና፣ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።”

13 በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሰራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሰራዊት በስተ ጀርባ እንዲያደፍጡ ላከ፤ የቀረውም ሰራዊት ከእርሱ ጋር የይሁዳን ሰራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙ አደረገ።

14 የይሁዳም ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከታቸውን ነፉ።

15 የይሁዳም ሰዎች በፉከራ የጦርነት ድምፅ አሰሙ፤ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ፊጽሞ መታቸው።

16 እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።

17 አብያና ሰዎቹም ከባድ ጒዳት አደረሱባቸው፤ ከዚህ የተነሣም ከእስራኤል ብርቱ ተዋጊዎች መካከል አምስት መቶ ሺህ ሰዎች ተገደሉ።