2 ዜና መዋዕል 14:6-12 NASV

6 በምድሪቱ ሰላም ስለ ሰፈነ፣ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔር ዕረፍት ስለ ሰጠውም፣ በዘመኑ የተዋጋው ማንም አልነበረም።

7 እርሱም ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ አላቸው፤ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ማማ፣ መዝጊያና መወርወሪያ ያላቸውን ቅጥሮች በዙሪያቸው እናብጅ። አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም የኛው ናት፤ እኛ ፈለግነው፤ እርሱም በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጠን” እነርሱም ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም።

8 አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የያዙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሰዎች እንዲሁም ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።

9 ኢትዮጵያዊው ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰራዊትና ሦስት መቶ ሠረገላ ይዞ በመውጣት እስከ መሪሳ ድረስ መጣባቸው።

10 አሳም ሊገጥመው ወጣ፤ መሪሳ አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆም የውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

11 በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደካሞችን ከኀይለኞች የሚታደግ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።”

12 እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት መታቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ፤