2 ዜና መዋዕል 16:1-6 NASV

1 አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ከእስራኤል ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ፣ ወደዚያም ማንም እንደይገባ ለመከልከል ራማን መሸገ።

2 አሳም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር ላከ፤

3 ከዚያም “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑረን፤ እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከባኦስ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው።

4 ወልደአዴር የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀበለ፤ የጦር አዛዦቹንም በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልማ ይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞች ሁሉ ድል አድርገው ያዙ።

5 ባኦስ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።

6 ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባንና ምጽጳን ሠራባት።