16 ከዚያም ሚካያ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሎአል” ሲል መለሰ።
17 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ ደግ ትንቢት እንደማ ይናገር አልነገርሁህምን?” አለው።
18 ሚካያም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
19 እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሬማት ገለዓድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ።
20 በመጨረሻም አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።
21 “እርሱም፣ ‘እሄድና በነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንግዲያውስ ሂደህ አሳስተው፤ ይሳካልሃልም’ አለው።
22 “አሁንም እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት አዞብሃል”።