2 ዜና መዋዕል 18:26-32 NASV

26 እነርሱንም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደህና እስክመለስም ድረስ ከደረቅ ቂጣና ከውሃ በስተቀር ምንም አትስጡት ብሎአል’ በሏቸው።”

27 ሚካያም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።

28 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ገለዓድ ወጡ።

29 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።

30 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዘዛቸው።

31 የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከእርሱ መለሳቸው፤

32 የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።