2 ዜና መዋዕል 18:6-12 NASV

6 ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

7 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ደግ ትንቢት ስለማይናገር እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚካያ ነው” ሲል መለሰ።ኢዮሳፍጥም፣ “ንጉሥ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።

8 የእስራኤልም ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “ሂድና የይምላን ልጅ ሚካያን በፍጥነት አምጣው” አለው።

9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

10 የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ” አለ።

11 ሌሎቹ ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በሬማት ገለዓድ ላይ አደጋ ጣልባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12 ሚካያን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ እየተነበዩ ነው፤ ያንተም ቃል እንደቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ተናገር” አለው።