2 ዜና መዋዕል 2:12-18 NASV

12 ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቶአልና።

13 “እጅግ ብልሃተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤

14 እርሱም እናቱ ከዳን ወገን፣ አባቱም የጢሮስ አገር ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በድንጋይና በዕንጨት፤ እንዲሁም በሐምራዊና በሰማያዊ፣ በቀይ ግምጃና በቀጭን በፍታ ሥራ የሠለጠነ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ልምድ ያካበተና የተሰጠውን ማናቸውንም ንድፍ በሥራ መተርጐም የሚችል ባለ ሙያ ነው። እርሱም ከአንተ የእጅ ሥራ ባለሙያዎችና ከጌታዬ ከአባትህ የእጅ ሥራ ባለ ሙያዎች ጋር አብሮ ይሠራል።

15 “አሁንም ጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት ስንዴውንና ገብሱን፣ የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ፤

16 እኛም የሚያስፈልግህን ግንድ ሁሉ ከሊባኖስ ቈርጠንና አስረን እስከ ኢዮጴ ድረስ ቍልቍል በማንሳፈፍ እንሰድልሃለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”

17 ሰሎሞን አባቱ ዳዊት ካደረገው ቈጠራ በኋላ፣ በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ ቈጠረ፤ ቊጥራቸውም አንድ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሆነ።

18 ከእነዚህም ሰባ ሺውን ተሸካሚዎች፣ ሰማንያ ሺውን በኰረብታው ላይ ድንጋይ ፈላጮች፣ ሦስት ሺህ ስድስት መቶውን ደግሞ የሥራው ተቈጣጣሪዎች ሆነው ሰዎቹን እንዲያሠሩ መደበ።