20 በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
21 ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሠራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣“እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ።
22 መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።
23 የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ።
24 የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም።
25 ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኮአቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ።
26 በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው።