2 ዜና መዋዕል 20:8-14 NASV

8 እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤

9 ‘የፍርድ ሰይፍም ሆነ የቸነፈር ወይም የራብ መከራ ቢደርስብን ስምህ በተጠራበት በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት፣ በፊትህ ቆመን በጭንቀታችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ትሰማናለህ፤ ታድነናለህም።’

10 እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ግዛታቸውን እንዳይወርሩባቸው በማድረግህ ከእነርሱ ተመልሰው ሳያጠፏቸው የቀሩት የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች እነሆ እዚህ አሉ።

11 እነሆ፣ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር እኛን በማፈናቀል ወሮታ ሊመልሱልን መጥተዋል።

12 አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።

13 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።

14 በዚህ ጊዜ የአሳፍ ዘር በሆነው በሌዋዊው በዘካሪያስ ልጅ፣ በየሕዚኤል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ። ዘካርያስም የበናያስ ልጅ ሲሆን፣ በናያስም የማታንን ልጅ የሆነው የይዒኤል ልጅ ነው።