10 ኤዶምም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው።ኢዮሆራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የልብና ከተማ በዚያኑ ጊዜ ዐመፀችበት።
11 ከዚህም በላይ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ መስገጃ ስፍራዎች ሠርቶ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚያ እንዲያመነዝር አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ።
12 ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤“የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤
13 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደሃል፤ የአክዓብ ቤት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያመነዝር እንዳደረገ ሁሉ፣ አንተም ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲያመነዝሩ አሳሳትሃቸው፤ እንዲሁም ካንተ የሚሻሉትን፣ የገዛ ወንድሞችህንና የአባትህን ቤተ ሰብ አባላት ገደልሃቸው፤
14 ስለዚህ እነሆ፤ እግዚአብሔር ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ያለህን ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይመታል።
15 አንተም ራስህ በየዕለቱ እየባሰ በሚሄድ የአንጀት በሽታ ክፉኛ ትታመማለህ፤ በመጨረሻም ሕመሙ አንጀትህን ወደ ውጭ ያወጣዋል።”
16 እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩ ዐረቦችን በኢዮሆራም ላይ በጠላትነት እንዲነሡ አደረገ።