2 ዜና መዋዕል 21:2-8 NASV

2 የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ።

3 አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮሆራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና።

4 ኢዮሆራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋር በሰይፍ ገደለ።

5 ኢዮሆራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

6 እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

7 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም የሚጸና መብራት እንዲኖር ለማድረግ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

8 በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።