1 ከዐረቦች ጋር ወደ ሰፈር የመጡት ወራሪዎች፣ ታላላቅ ወንድሞቹን ሁሉ ገድለዋቸው ስለ ነበር፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ የኢዮሆራምን የመጨረሻ ልጅ አካዝያስን በአባቱ ምትክ አነገሡት። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ መግዛት ጀመረ።
2 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ የልጅ ልጅ ነበረች።
3 እናቱ ክፋትን እንዲያደርግ ትመክረው ስለ ነበር፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ።
4 ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለ መሩት፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
5 እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም የሶርያን ንጉሥ አዛሄል ለመውጋት ወደ ሬማት ገለዓድ በሄደ ጊዜ የእነዚህኑ ሰዎች ምክር ተከትሎ ከኢዮራም ጋር አብሮት ሄደ፣ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት።