2 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ የልጅ ልጅ ነበረች።
3 እናቱ ክፋትን እንዲያደርግ ትመክረው ስለ ነበር፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ።
4 ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለ መሩት፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
5 እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም የሶርያን ንጉሥ አዛሄል ለመውጋት ወደ ሬማት ገለዓድ በሄደ ጊዜ የእነዚህኑ ሰዎች ምክር ተከትሎ ከኢዮራም ጋር አብሮት ሄደ፣ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት።
6 ስለዚህ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሬማት ላይ ከደረሰበት ቍስል ለመዳን ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በመቍሰሉም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
7 አካዝያስ ኢዮራምን ለመጠየቅ መሄዱን፣ እግዚአብሔር ለአካዝያስ መውደቅ ምክንያት አደረገው፤ አካዝያስ እንደ ደረሰም የናሜሲን ልጅ ኢዩን ለመቀበል ከኢዮራም ጋር ወጣ፤ ኢዩም የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ እግዚአብሔር የቀባው ሰው ነበር።
8 ኢዩ በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድ በሚፈጽምበት ጊዜ፣ አካዝያስን ያጅቡ የነበሩትን የይሁዳን መሳፍንትና የዘመዶቹን ወንዶች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው።