2 ዜና መዋዕል 23:3-9 NASV

3 ጉባኤው ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ።ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለዳዊት ዘር በሰጠው ተስፋ መሠረት እነሆ፣ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል።

4 እንግዲህ እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ዕለት ተረኛ ከሆናችሁት ከእናንተ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ አንድ ሦስተኛው በሮቹን ጠብቁ፤

5 አንድ ሦስተኛው ቤተ መንግሥቱን፣ አንድ ሦስተኛው “የመሠረት ቅጽር በር” የተባለውን ጠብቁ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ይሁኑ።

6 ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ።

7 ሌዋውያኑም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ይቁሙ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረውት ይሁኑ።”

8 ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤

9 ከዚያም በቤተ መቅደሱ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ታላላቅና ታናናሽ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።