2 ዜና መዋዕል 24:21-27 NASV

21 እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

22 ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ።

23 በዓመቱም መጨረሻ፣ የሶርያ ሰራዊት በኢዮአስ ላይ ዘመተ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም ወሮ የሕዝቡን መሪዎች ሁሉ ደመሰሰ፤ ምርኮውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላከ።

24 የሶርያ ሰራዊት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር በጣም የሚበልጠውን ሰራዊት በእጃቸው አሳልፎ ሰጠ፤ ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ በኢዮአስ ላይ ተፈረደበት።

25 ሶርያውያንም በወጡ ጊዜ ኢዮአስን ክፉኛ አቍስለው፣ ጥለውት ሄዱ፤ የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ስለ ገደለም፣ ሹማምቱ አሢረውበት በዐልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በዳዊት ከተማ ተቀበረ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልተቀበረም።

26 በእርሱ ላይ ያሤሩትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቱ የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ።

27 የወንዶች ልጆቹ ታሪክ፣ ስለ እርሱ የተነገሩት ብዙ ትንቢቶችና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መታደስ በነገሥታቱ የታሪክ መዛግብት ተጽፈዋል። ልጁ አሜስያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።