2 ዜና መዋዕል 24:9-15 NASV

9 ከዚህ በኋላ እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ።

10 ሹማምቱ ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ግብሩን በደስታ አመጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጨመሩ።

11 ሣጥኑ በሌዋውያኑ እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በሚደርስበት ጊዜ፣ እነርሱም በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም ይመጡና ሣጥኑን አጋብተው ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። ይህን በየቀኑ በማድረግ እጅግ ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ።

12 ንጉሡና ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን አስረከቧቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ድንጋይ ጠራቢዎችንና ዐናጢዎችን እንዲሁም ቤተ መቅደሱን ለመጠገን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ቀጠሩ።

13 በሥራው ላይ የተሰማሩት ሰዎች ትጉሃን ስለ ነበሩ፣ ሥራው በእጃቸው ተከናወነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀደም ሲል በነበረው ዐይነት መሠረት ዐደሱት፤ አጠናከሩትም።

14 ከጨረሱም በኋላ ቀሪውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ በገንዘቡም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ማለትም ለአገልግሎትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚውሉ ዕቃዎች እንደዚሁም ጭልፋዎችና ሌሎች የወርቅና የብር ዕቃዎችም ተሠሩ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ይቀርብ ነበር።

15 ዮዳሄ ሸምግሎ ዕድሜ ከጠገበ በኋላ በመቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ።