2 ዜና መዋዕል 26:5-11 NASV

5 እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።

6 በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።

7 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው።

8 አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብፅ ዳርቻ ወጣ።

9 ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማዕዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው።

10 እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጒድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሰራተኞች ነበሩት።

11 ዖዝያን ከንጉሡ ሹማምት አንዱ በሆነው በሐናንያ መሪነት፣ በጸሓፊው በይዒኤልና በአለቃው በመዕሤያ አማካይነት ተሰብስቦ በተቈጠረው መሠረት በየምድቡ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚወጣ፣ በሚገባ የሠለጠነ ሰራዊት ነበረው።