11 እንግዲህ ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቊጣ በእናንተ ላይ ነዶአልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”
12 ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣
13 “እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ ያለዚያ እኛ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቶአል፤ ቊጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።
14 ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ።
15 በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቁታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16 በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤
17 ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና።