2 ዜና መዋዕል 28:20-26 NASV

20 የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም።

21 አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።

22 ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤

23 እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ።

24 አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማዕዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።

25 በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ አነሣሣው።

26 በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና አካሄዱ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።