4 በኰረብታ መስገጃዎችና በተራሮች አናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።
5 ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ አልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጒዳት አደረሰበት።
6 ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ወታደሮች ገደለ።
7 ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
8 እስራኤላውያንም ከገዛ ወገኖቻቸው ሁለት መቶ ሺ ባለ ትዳር ሴቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
9 ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቊጣ ፈጃችኋቸው።
10 አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አልበደላችሁምን?