2 ዜና መዋዕል 29:21-27 NASV

21 እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ።

22 ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት።

23 ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው።

24 ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፣ ካህናቱ ፍየሎቹን ዐርደው ስለ እስራኤል ሁሉ ማስተስረያ እንዲሆን የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ደሙን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።

25 ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።

26 ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።

27 ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ።