25 ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።
26 ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።
27 ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ።
28 መዘምራኑ በሚዘም ሩበትና መለከተኞቹም በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ አጎንብሰው ሰገዱ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉ ቀጠለ።
29 መሥዋዕቱ ሁሉ ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሁሉ ተንበርክከው ሰገዱ።
30 ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጎንብሰው ሰገዱ።
31 ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።