2 ዜና መዋዕል 29:5-11 NASV

5 እንዲህ አላቸው፤ “እናንት ሌዋውያን፤ ስሙኝ! ራሳችሁን አሁኑኑ ቀድሱ፤ የአባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀድሱ። ርኩስ ነገርንም ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።

6 አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ተውትም። ከእግዚአብሔር ማደሪያ ፊታቸውን መለሱ፤ ጀርባቸውንም አዞሩበት።

7 የሰበሰቡንም በሮች ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ። ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ዕጣን አላጠኑም፤ በመቅደሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አላቀረቡም።

8 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወርዶአል፤ እናንተ በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት ለድንጋጤ፣ ለመደነቂያና ለመዘበቻ አሳልፎ ሰጣቸው።

9 በዚህ ምክንያት አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችንም ተማረኩ።

10 አሁንም አስፈሪ ቊጣው ከእኛ እንዲመለስ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት አስቤአለሁ።

11 ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”